የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 5 እንደሚከበር ተገለጸ


ጥቅምት 2/2016 (አዲስ ዋልታ) የሰንደቅ ዓላማ ቀን “የሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና ለሉዓላዊነታችን ዋስትና ነው” በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 5 እንደሚከበር ታውቋል፡፡

በዓሉ በሀገራችን ለ16ኛ ጊዜ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታን በዋጀ መልኩ ፤ ከሰንደቅ ዓላማ መርሆች ጋር ተገናዝቦ እና ሀገራዊ ሪፎርሙን በሚያስቀጥሉ ውይይቶች ታጅቦ በሕዝብ ተወካዮቸ ምክር ቤት መሪነት በመላ ሀገሪቷ እንደሚከበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

ምክር ቤቱ ጥንት እናት እና አባቶቻችን የሀገራችንን ዳር ድንብር ደፍሮ የሀገር ነጻነትና ሉዓላዊነትን ለመውሰድ በየዘመናቱ የመጣን የውጭ ወራሪ ኃይል መክተው በከፈሉት ሕይወት መስዋዕትነት ነጻነታችን ተጠብቋል ብሏል፡፡

ሰንደቅ ዓላማችን ተገቢውን ክብር ይዞ ከትውልድ ትውልድ ተላልፎ እነሆ ከአሁኑ ትውልድ መድረሱም ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

የበዓሉ መከበር ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን እና ለሉዓላዊነታን መጠናከር መነቃቃትን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡

ለሃገር ክብር እና ጥቅም ሁሉም የበኩሉን ለመወጣት በሰንደቅ ዓላማ ፊት ዳግም ቃላል የሚያድስበት ዕለትም ይሆናል ብሏል ምክር ቤቱ ፡፡

በዓሉ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኤምባሲዎች እና የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በተመሳሳይ ሰዓት ከረፋዱ 4 ሰዓት ተኩል ላይ በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ የመጀመሪው ሰኞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንደሚከበር በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 863/2006 አንቀጽ 2 ተደንግጎ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡