የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ወረራን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ከ1997 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በከተማዋ 1ሺህ 300 ሄክታር መሬት በህገ ወጥ ወረራ መያዙን አስታወቀ፡፡
በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ 121 ወረዳዎች 88 ወይም ደግሞ 73 በመቶ የሚሆነው ይዞታ ህገ ወጥ ወረራ ተፈፅሞበታል ብሏል ከተማ አስተዳደሩ።
ከለውጡ በፊት በርካታ ህገ ወጥ የመሬት ወረራዎች ሲፈፀሙ እንደቆዩ በመግለጫው ላይ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከለውጡ በኋላም ያለው አመራር ህገወጥነት በተገቢው መልኩ ባለመከላከሉ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል ብለዋል።
ባለቤት አልባ ህንፃና ቤቶችን በከተማዋ 322 የተገኙ ሲሆን አጠቃላይ ስፋታቸው ደግሞ 226ሺህ 556 መሆኑ ተለይቷል ብለዋል። ባለቤት አልባ ሲባልም ባለቤታቸው ያልታወቁና ያልተገኙ ናቸው ብለዋል።
የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ በአራት መንገዶች የማጥራት ስራ ተሰርቷል ያሉት ም/ከንቲባዋ በተደረገው ጥናት መሰረትም በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ህገ ወጥ ኮንዶሚኒየሞች ከ15ሺህ 891 ቤቶች መረጃ ያልቀረበባቸውና በህገወጥ መንገድ የተያዙ ሲሆኑ 4ሺህ 530 ቤቶች ባዶ የሆኑና 850 ዝግ የሆኑ ቤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
ከቀበሌ ቤት ጋር የቀበሌ ህጉ ከሚፈቅደው ውጪ 7ሺ 723 ቤቶች ውል በሌላቸው ህገወጦች መያዛቸውን ም/ከንቲባዋ ገልፀዋል።
በጥናቱ የተገኘው ግኝት ህገወጥ ወረራን በተመለከተ 1997 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ለውጡ ድረስ የተፈፀመ ነው ብለዋል።
ህገወጥነትን ለፖለቲካ ባለማዋል ለፍትሀዊ ተጠቃሚነት መሰራቱ ለህዝብ ለሀገርም ጠቃሚ ነው ብለዋል።
በተገኘው ግኝት መሰረትም አብዛኛውን ህገ ወጥ ወደ መሬት ባንክ መመለሱና ይህ ሁሉ ሲፈፀም የነበሩ አመራሮች በህግ እንዲጠየቁ ለፌደራል ፖሊስና ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ተልኳል ብለዋል።
በቀጣይ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር እንሰራለን ብለዋል።
(በሱራፌል መንግስቴ)