ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “በጎነት ለዘላቂ አብሮነት እና ወንድማማችነት” በሚል መሪ ቃል በመጪው የክረምት ወራት በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር 570 ሺሕ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማቀዱ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስፋው ተክሌ በሰጡት መግለጫ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ሰው ተኮር ተግባራቶችን በልዩ ሁኔታ ለመምራት እንዲያስችል ተደርጎ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በሰባት ዋና ዋና ተግባራትና በ14 ንዑሳን ተግባራት ተከፋፍሎ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን በጎ ፈቃደኞችን በታቀዱ ተግባራት ላይ በማሳተፍ 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የመንግሥት ወጪን ለማዳን ከተማ አስተዳደሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሁሉም ሰው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አካል እንዲሆንም ጥሪ መደረጉን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።