በምርጫ ቦርድ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ቦርድ ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

መድረኩ የቦርዱ ሰበሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የፓርቲዎቹን መገኘት አመስግነው፤ ፓርቲዎቹ በረቂቅ መመሪያዎቹ ላይ ያላቸውን ገንቢ አስተያየቶች እንዲያካፍሉ ጥሪ አድርገዋል።

ረቂቅ መመሪያዎቹ ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 57 ንዑስ አንቀጽ 4 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ነው መድረኩን ያካሄደው፡፡

በዚህም የድምፅ አሰጣጥን፣ ቆጠራንና የምርጫ ውጤት አገላለጽ ሂደት አፈጻጸምን ግልጽና ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የዕጩ ወኪሎች፣ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች፣ የሀገር ውስጥና የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች በነዚህ ሂደቶች ላይ ወጥነት ያለው አሠራር እና በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ተብሎ የተዘጋጁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ይህንንም በማስመልከት የመድረኩም አቅራቢ የሆኑት ዶክተር ጌታቸው አሰፋ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ፣ የወጪና የንብረት አስተዳደር እና ሪፖርት አቀራረብ መመሪያና የድጋሚ ምርጫ አፈጻጸምን የተመለከቱት ረቂቅ መመሪያዎችን ጨምሮ የመድረኩ አቅራቢ በሆኑት ባለሞያዎች በዶክተር ጌታቸው አሰፋ፣ ሰለሞን ግርማና ዳኛቸው መለሰ ማብራሪያ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

ማብራሪያዎቹን ተከተሎ በሁለት ዙር ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጋር የቦርዱ አመራር በሆኑት አቶ ውብሸት አየለ መድረክ መሪነት የፓርቲ ተወካዮቹ ሀሳብና አስተያየት እንዲሰጡበት ተመደረጉም ተጠቅሷል፡፡

ፓርቲዎቹም በመድረኩ እንዲብራራላቸው የፈለጉትን አንቀጽና ቢጨመር ያሉትን ሀሳብ ማጋራታቸው ተገልጿል፡፡

ይህንንም ተከትሎ ባለሞያዎቹ የፓርቲ ተወካዮቹ ባቀረቧቸው አስተያየቶች መሠረት ማብራሪያ ሰጥተውበታል።
ፓርቲዎቹ የሚኖራቸውን አስተያየቶች በመድረኩ ሳይወሰኑ በጽሑፍም ማቅረብ እንደሚችሉ ባለሞያዎቹ ገልጸዋል።

(ምንጭ፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ)