ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች የክልሉን ሰላምና ገፅታን በሚገነባ መልኩ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡
በክልሉ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የሶማሌ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ በደል የሶማሌ ክልል ሕዝብ ለ27 ዓመታት በፖለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የነበረ ሕዝብ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለውጡን ተከትሎ በተገኘው ውጤት ሶማሌ ክልል ሰላም የሰፈነበት ክልል ሆኗል፣ ይህንን እድል በመጠቀም በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደ መንግሥትም ሰላሙን ዘላቂ ለማድረግ የገጠሙ ተግዳሮቶች በየደረጃው እየፈታን ነው ብለዋል::
ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት የሆነው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መስፋፋት፣ ወሰን አካባቢ በአንዳንድ ቦታዎች ጥቃቅን ግጭቶች መኖርና በፅንፈኝነት አስተሳሰብ የተቃኙ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወቅታዊ ተግዳሮቶች ቢሆኑም ይህንን በመቋቋም 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በክልሉ በሚገኙ 93 ወረዳዎችና በስድስቱም ከተሞች ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያለምንም እንቅፋት ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል::
በክልሉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተመለከተ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደ መንግሥት ተወስዷል ያሉት አቶ አሊ፣ ጤና ሚኒስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባወጡት መመሪያ መሰረት የኮቪድ ፕሮቶኮሎች ተግባራዊ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ነው ብለዋል፡፡
ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በትራንስፖርት፣ በግብይት ስፍራዎች፣ በምርጫ ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅት አፍንጫ እና አፍ መሸፈኛ እንዲያደርጉ፣ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ፣ ሆቴል አካባቢ በሚደረጉ ሁነቶችም በሕጉ መሰረት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል::
በአጠቃላይ በክልሉ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የማይካሄድበት ቦታ የለም ያሉት ኃላፊው፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ በክልሉ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ኃይሎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውንና ፖለቲካ አጀንዳቸውን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
በመጨረሻም የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በጋራ በመስራት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀው፤ ምርጫው እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም ባላድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢፕድ ዘግቧል::