በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር የመተከል ተፈናቃዮችን ጎበኙ

 

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር

የካቲት 11/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄኒሪክ ላንድኩስት እና የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ክሆድር የመተከል ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።

አምባሳደር ሀንስ ሄኒሪክ ላንድኩስት እና የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ክሆድር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈናቀሉ እና በአማራ ክልል ቻግኒ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ነው የጎበኙት፡፡

ቻግኒ በሚገኘው መጠለያ ጣቢያ በአሁኑ ሰዓት 43 ሺህ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

በመተከል ዞን በተፈጠረው ግጭት ከ70 ሺህ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉ ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በመረጃው ጠቅሷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህፃናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) ከኢትዮጵያ መንግስትና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ለተፈናቃዮች የጤና አገልግሎት፣ አልሚ ምግብ፣ የውሃና የንጽሕና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።

የስዊድን አለም አቀፍ የልማት ትብብር ኤጀንሲ(SIDA) ከዪኒሴፍ ጋር በመተባበር በ2020 6 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።
(ምንጭ ፡-ኢዜአ)