የካቲት 25/2015 (ዋልታ) በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት በሀገራዊ ዕድገትና ገጽታ ግንባታ ላይ ጠንካራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ መከናወኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተዘጋጀው የፌዴራልና ክልል ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማት የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ እየተካሄደ ነው።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ በጫናዎች ውስጥ ሆናም በተለያዩ ማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል።
በኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር ስራዎች፣ በአገልግሎት አሰጣጥና በዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንደ ሀገር የተመዘገቡ ስኬቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በመንግሥትና ህወሐት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት እንዲይዝ እንዲሁም በሌሎች ሀገራዊ ስኬቶች ላይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጠንካራ ስራ አከናውኗል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ውስብስብ ችግሮችን በመፍጠር ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የገለፁት ሚኒስትሩ፣ ይሄንን በመመከትም አበረታች ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በቀጣይም አክራሪነትና ፅንፈኝነትን በቅንጅት በመመከት የኢትዮጵያን ህዝብ የሚመጥን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራ መስራት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡