ሰኔ 08/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያና አልጄሪያ በታዳሽ ኃይል እና ኢነርጂ ስርጭት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለጸ፡፡
በአልጀሪያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ከአልጀሪያ የኢነርጂ ማስፋፊያ እና ታዳሽ ሃይል ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሸመስ ኢዴን ሺቱር ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይቱ በሁለቱ አገራት መካከል በታዳሽ ኃይል እና ኢነርጂ ስርጭት ዘርፍ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል፡፡
አምባሳደር ነብያት ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ የኃይል እቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት በታዳሽ ሃይል የኢነርጂ ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ለኢትዮጵያ ህዝቦች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማሟላት መንግስት የታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ፣ የንፋስ፣ የፀሐይ እና ጂኦ ተርማል የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና የድርድር ሂደትን አስመልክቶም አምባሳደሩ ለሚኒስትሩ ገለፃ ያደረጉላቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ጋር ያሉትን ልዩነቶች በውይይትና በድርድር ለመፍታትና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ሀብቶቿን ለማልማት የምታደርገውን ጥረት አልጀሪያ እንደምትደግፍና በዘርፉ ያላትን ልምድ በስልጠናና በአቅም ግንባታ በትብብር ለመሥራት ያላትን ዝግጁነት መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡