ኮሮና ቫይረስን በደም ውስጥ ለመመርመር የሚያስችል የህክምና ዘዴ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለፀ

ሚያዝያ 15/2013 (ዋልታ) – የኮሮና ቫይረስን በደም ውስጥ ለመመርመር የሚያስችል የህክምና ዘዴ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለፀ።

ስካት የተሰኘው እና በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የተገኘው የመመርመሪያ መሳሪያ በግለሰብ ውስጥ የሚገኝን የቫይረሱን የመቋቋም አቅም የሚያሳይ ነው ተብሏል።

በአርሞር ሀንሰን የምርምር ተቋም እና ሀርቨርድ ዩኒቨርስቲ ትብብር ለአገልግሎት የበቃው አዲሱ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪት በአንድ ግለሰብ ደም ውስጥ ያለውን በሽታ የመከላከል አቅም በመለካት የቫይረሱን መኖር እና የግለሰቡን የመከላከል አቅም እንደሚያሳይ ተገልጿል።

ስካት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ጋር በክልሉ በሚገኙ ተማሪዎች ላይ ተሞክሮ አመርቂ ውጤት ማሳየቱን የገለፁት በአርሞር ሀንሰን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ተስፋየ ገላና፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ እና የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ባለባቸው አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለማወቅ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረው የምርመራ ሂደት እንዳለ ሆኖ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የስርጭቱን ተስፋፊነት ለመገመት ይረዳል የተባለለት አዲሱ የኮቪድ-19 ሳይንሳዊ መመርመሪያ መሳሪያ በቀጣይ በስፋት አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሏል።
(በቁምነገር አህመድ)