መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – ወጣቶች በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን ተጽዕኖ በውል በመረዳት ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም ለማሳወቅ በዲጅታል ሚዲያው በስፋት እንዲንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሠላም በጎ ፈቃደኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዮሐንስ ጣሰው ጥሪ አቀረቡ።
ዲጅታል ሚዲያው በዓለም ላይ ያለው ኃይልና የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ ጣሰው፣ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግብ እንዳይደርስ እየሠሩ ያሉ ወገኖች ዓለም ለግድቡ ያለው እይታ የተዛባ እንዲሆን እርብርብ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ዲጅታል ሚዲያ ቀላል ጊዜ፣ ቀላል ጉልበትና ቀላል ሀብት በመጠቀም ሃሳባችንን ለዓለም ማድረስ የሚያስችል በመሆኑ ወጣቶች ሁሉንም ዓይነት አማራጮች በመጠቀም መሬት ላይ ያለውን እውነትና ትክክለኛውን የአገሪቱ ገጽታ ዓለም እንዲገነዘበው ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
የዓባይ ጉዳይ በተለያዩ ዘመናት በነበሩ ወጣቶች ልብ ውስጥ የነበረና በምን መልኩ ተጠቅመን የአገራችንን እድገት እናፋጥን የሚለው እንቆቅልሽ ሳይፈታ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ላይ ያሉ ወጣቶች ዕድለኛ ሆነው ሌሎቹ ሲያዜሙለትና ሲቀኙለት ብንሠራው፣ ብንገድበው ይችን አገር ብናሳድግበት የሚለውን ህልማቸውን በቀጥታ ወደ ተግባር ይዞ የገባ ትውልድ አካል መሆን መቻሉን ገልጸዋል።
ይህን የትውልዶች ሁሉ የዘመናት ህልምና ቁጭት የነበረውን ዓባይ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ሩጫ በፖለቲካና በሌሎችም አጀንዳዎች ምክንያት ሳይዘናጉ ግንባታው ሲጀመር በነበረው ግለት ልክ መደገፍ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።
በግንባታው እየተሳተፉ ያሉት ባለሙያዎች አብዛኞቹ ወጣቶች መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣ ዘርፈ ብዙ የሆነውን ተሳትፏቸውን አጠናክረው በመቀጠል በመገባደድ ላይ የሚገኘውን ግድብ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትጵያ ወጣቶች ስግብግቦች አይደሉም፤ ከተፋሰሱ አገሮች ወጣቶች ጋር ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይህን ግድብ ለመጠቀም አያመነቱም፤ ይህንን የምናረጋግጠው ከተለያዩ የዓለም አገሮች የሚመጡ ወጣቶችን እንዴት አድርገው እንደሚቀበሉ፣ እንዴት አድርገው ተግባብተውና ተዋህደው ውለው እንደሚያድሩ ሲታይ ነው ብለዋል።
ስለሆነም ሌሎች አገሮች በግድቡ ግንባታ ምክንያት ጉዳት ይደርስብናል ብለው መስጋት የለባቸውም ማለታቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል።