የካቲት 24/2015 (ዋልታ) የነዳጅ ግብይት ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት ለማድረግ ትግበራ መጀመሩን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
1 ሺሕ 24 ተሽከርካሪዎች ወደ ቴሌብር ሥርዓት መግባታቸው እና የኤሌክትሮኒክስ ግብይት መተግበሪያ የሌላቸው ተጠቃሚዎች ዝግጁ እንዲሆኑ የገለጸው ሚኒስቴሩ በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልጿል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ክፍያ መፈፀም የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን እና የነዳጅ ድጎማውን በመቆጣጠር የኢኮኖሚ ጫና እንዳይፈጠር ያደርጋል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው ለነዳጅ ድጎማ 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ መውጣቱን ገልጸው በቀጣይ ድጎማውን ለማስቀረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በብርቱካን መልካሙ