የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር የትብብር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ


መስከረም 23/2016 (አዲስ ዋልታ) የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ለሚገኙ የለውጥ ስራዎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕብረቱ የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን አስታወቁ፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ከአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ጋር መወያየታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በውይይታቸውም የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ አጋር መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ሚኒስትሯ ሕብረቱ እስካሁን ላደረጋቸው የትብብር ተግባራት ምስጋና አቅርበዋል።

የዚሁ ትብብር አካል የሆነው የ650 ሚሊዮን ዩሮ የድጋፍ ማዕቀፍ ይፋ በመሆኑም ሚኒስትሯ አመስግነዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ሕብረቱ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና ግብርና ስራዎች፣ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ አረንጓዴ ልማት፣ አካባቢ ጥበቃና ታዳሽ ኃይል ልማት፣ ለሰው ኃይል ልማት፣ በጤና፣ በመልካም አስተዳደር፣ ሰላም ግንባታና የዴሞክራሲ ልማት ስራዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።