በሐረር ከተማ ሽንኩርትን በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ የተገኙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

መስከረም 23/2016 (አዲስ ዋልታ) በሐረር ከተማ ቀይ ሽንኩርትን በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ በተገኙ 17 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ንግድ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው ስራ ኃላፊ ሸሪፍ ሙሜ እንደገለፁት በክልሉ በሸቀጦች፣ በኢንዳስትሪና በግብርና ምርቶች ላይ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ክትትል እየተደረገ ነው።

በዚህም በዛሬው እለት በከተማው በተለምዶ ደከር በተባለው የገበያ ስፍራ በተደረገ ክትትል 17 የንግድ ጅምላ አከፋፋይና ቸርቻሪ ነጋዴዎች ቀይ ሽንኩርት በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ መገኘታቸው ገልፀዋል።

በዚህም የጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች ማከማቻና መሸጫ ስፍራቸው የማሸግ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

ነጋዴዎቹ ቀደም ሲል አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት እስከ 85 ብር ይሸጡ እንደነበር አስታውሰው ሰሞኑን በአሁኑ ወቅት ግን እስከ 130 ብር ድረስ ሲሸጡ በመገኘታቸው እርምጃው ተወስዶባቸዋል ነው ያሉት።

እርምጃው ከተወሰደባቸው ነጋዴዎች መካከል 3 ነጋዴዎች እያንዳንዳቸው 20ሺ ብር እንዲቀጡ መደረጉን፣ 5ቱ በህግ አግባብ ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝና ቀሪው ደግሞ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ነጋዴዎቹ የክልሉ ንግድ ጽህፈት ቤት በለጠፈው ዋጋ ለመሸጥ እስካልተስማሙ ድረስ እርምጃው እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ ሸሪፍ በቀጣይም ዋጋ በሚጨምሩ ሌሎች ነጋዴዎች ላይ እርምጃው ተጠናከሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ማህበረሰቡ ከተመን በላይ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ሲመለከት ለግብረ ሃይሉ ሊጠቁም እንደሚገባ ኃላፊው መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡