የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ ካቶሊከዊት ቤተክርስቲያን የ510 ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈራረሙ

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ካቶሊከዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የ510 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የኢትዮጵያ ካቶሊከዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል ጋር ተፈራርመዋል ።
በአዲስ አበባ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በከተማ አስተዳደሩ ጥረት ብቻ መፍታት እንደማይቻል የገለፁት ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቤተክርስቲያኗ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸውን ለመቅረፍ የጀመረችውን ስራ አጠናክራ መቀጠል አለባት ብለዋል፡፡
ቤተክርስቲያኗ በከተማው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ለያዘችው እቅድ በከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ ከተማሪዎች ጀምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ዜጎችን ለመመገብ የጀመራቸውን ስራዎች የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል ።
በትብብር የሚሰሩት ስራዎች በአጠቃላይ 510 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚደረግባቸው ሲሆን በቀን 150ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ያለው የዳቦ ማምረቻ፣ የትምህርትን ሽፋንና ጥራት በማረጋገጥ የሚያግዙ 8 የመዋለ ህጻናት፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን እና የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ግንባታ፣ የተለያዩ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያግዙ የክህሎት ስልጠናዎች የሚሰጡበት የወጣቶች ሁለገብ ማዕከል ሥራ እንደሚገኙበት ስምምነቱ ላይ መገለጹን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።