ሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት መሰረት እየጣለ መሆኑ ተገለጸ

ሚያዝያ 21/2013 (ዋልታ) – ሳምንታዊው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የውይይት መድረክ “የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ፈተናዎቹ” በሚል ዛሬ ተካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪው ዶክተር ግርማ አመንቴ በክልሉ ገጠርን የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሰራው ሥራ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልፀዋል፡፡

ለገጠር ሴክተር ፋይናንስ በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ ለአርሶአደሩ ብድር ተመቻችቶ ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ የግብርና ቴክኖሎጂ ከውጭ እንዲያስገቡ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በመድርኩ ላይ የመወያያ ሀሳብ ያቀረቡት የፕላንና ልማት ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ዶክተር ነመራ ማሞ ሀገር በቀሉ የኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት መሰረት እየጣለ ነው ብለዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ቀውስ ተቋቁሞ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቡ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለውጥ እያስመዘገበ ስለመምጣቱ ማሳያነውም ብለዋል ዶክተር ነመራ፡፡

የዋጋ ግሽበት አይነት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የገጠመውን ፈተና ለመሻገር በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ምርታማነትን ማሳደግ አሁን ሀገሪቱ ለገጠማት የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት ችግርን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ የተገለጸ ሲሆን አምራች ለሆኑ ሴክተሮች የፋይናንስ ብድር በማቅረብ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሁነኛ መፍትሄ ነው ተብሏል፡፡
(በአሳየናቸው ክፍሌ)