ሀገር አቀፍ የትምህርት ብርሃን ምዘና መርሀ ግብር በይፋ ተጀመረ

አቶ ደመቀ መኮንን

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ብርሀን ምዘና መርሀ ግብርን በይፋ አስጀምሯል።

የትምህርት ብርሀን ምዘና የሀገርን የመማር ምጣኔ የሚያሳድግ በመሆኑ የተማረ የሰው ሃይልን የማፍራት ተልዕኮን መወጣት እንደሚገባ ተገልጿል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የምዘና ስርዓቱ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች እውቀትን ያገኙ ዜጎችን በማነቃቃት ሌሎች ዜጎችም ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ እና መደበኛ እውቀት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ህዝቡ ይህንን እድል እንዲጠቀምበት ጥሪ በማስተላለፍ መርሀ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) የትምህርት ብርሀን ምዘና የትምህርት ዘርፉ አንዱ የለውጥ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ላይ ያሉ ማንበብ፣ መፃፍ እና ማስላት የሚችሉ ነገር ግን ያልተመዘኑ እና እውቅና ያላገኙ ዜጎች ተመዝነው እውቅና እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።

መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች ትምህርትን በመስጠት የሀይማኖት ተቋማቶች ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየታቸውን እና በዚህም ማንበብ፣ መፃፍ እና ማስላት የሚችሉ ዜጎች መፈጠራቸውን ሚነስትሩ ተናግረዋል።

ንቅናቄው ቀጣይነት ያለው እና ሁሉም ማንበብ እና መፃፍ የሚችል ዜጋ በዚህ የምዘና ስርዓት በማለፍ በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።

በመረሀ ግብሩ ላይ የህዝብ ተወካዬች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የክልል አመራሮች ፣የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።