የፌደራል መንግስት ተግባር ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ፣ ህግና ስርዓት ማስከበርና መልሶ ማቋቋም ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት የሚያከናውናቸው ተግባራት ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ ህግና ስርዓት ማስከበርና መልሶ ማቋቋም መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ጽሕፈት ቤቱ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር እርምጃው ንጹሃን ዜጎች ሳይጎዱና ንብረቶች ሳይወድሙ የመቐለ ከተማን በመቆጣጠር እርምጃው መጠናቀቁን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት ተግባራት ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ፣ በአካባቢው ሕግና ስርዓት እንዲኖር እንዲሁም መልሶ ማቋቋም መሆኑም ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።

እንዲሁም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያገኙ፤ ከአካባቢያቸው ርቀው ድንበር አቋርጠው የተሰደዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና በወንጀለኛው ቡድን የፈረሱና አገልግሎት ያቋረጡ የትራንስፖርትና መገናኛ መሰረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው የገለጸው።

የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ዕድገት፣ ሰላም፣ ነጻነትና ደህንነት ቢሆንም የህወሓት ጁንታ ቡድን በፍትሃዊና እኩልነት የተመሰረተች ኢትዮጵያን ለመመስረት አጋር መሆን የማይችል እንደሆነም አውስቷል፡፡

ቡድኑ ከተጠያቂነት ለማምለጥ መንግስት የወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ በተመለከተ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጣልቃ ገብተው ድርድር እንዲደረግ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱም ተመልክቷል።

የጁንታው ህወሓት ቡድን በሚገባ የተሸነፈ እና የደፈጣ ውጊያ ለማድረግ ምንም አቅም የሌለው መሆኑ እየታወቀ ቡድኑ ግን ከእነሙሉ አቅሙ እንዳለና ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ የደፈጣ ውጊያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የሚያትቱ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሲነዛ መቆየቱንም ጽሕፈት ቤቱ አስታውሷል።

ቡድኑ ዓለም የተለያዩ የሐሰት ውንጀላዎችን በማቅረብና የሕግ ማስከበር ዘመቻው ዓለም አቀፍ መልክ እንዲይዝና ከተጠያቂነት ለመምለጥ ጉዳዩ ወደ ድርድር እንዲወሰድ ፍላጎት አሳይቶ እንደነበርም አስታውቋል።

የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙም ባሻገር በማይካድራ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ፣ እንዲሁም ወደ ባህርዳርና ጎንደር ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ መላኩ ለሰላማዊ ዜጎች ምንም ግድ የሌለው ቡድን መሆኑን ግልጽ ያደርጋል ብሏል ጽሕፈት ቤቱ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማብራሪያው መንግስት በማንኛውም ጊዜ ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑንም አረጋግጧል።

በትግራይ ክልል በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንዲሁም በክልሉ በስደተኞች ካምፕ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ ስደተኞች ድጋፍ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግስት ከሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትና ከመንግስታቱ ድርጅት ኤጀንሲዎች ጋር በትብብር እየሰራ ነውም ብሏል፡፡