ህልውናችን ለሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋችን ይቀጥላል- ባለሀብቶችና የመንግስት ሰራተኞች

መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – ህልውናችን የሆነው የህዳሴው ግድብ ግንባታ እሰኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የድሬዳዋ ከተማ ባለሀብቶችና የመንግስት ሰራተኞች ገለጹ።

በከተማዋ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ወደ ጅቡቲ በመላክ የሚተዳደሩት ወይዘሮ መይሙና እድሪስ ግድቡ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ የሚያደርስና ልጆቻችን ከድህነት የተላቀቀች ሀገር እንዲወርሱ የሚያስችል በመሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል።

“በልጆቼና በራሴ ሶስት ጊዜ ቦንድ ገዝቻለሁ፤ ዘንድሮም ለመግዛት ተዘጋጅቻሁ” ሲሉም አክለዋል።

የሸሙ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ እስኪያጅ አቶ ተስፋሚካኤል ጉኡሽ በበኩላቸው፣ ግድቡ ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር የምጣኔ ሃብት መዋቅራዊ ሽግግር ለማድረግ የሰነቀችው ራዕይ ትርጉም ባለው መንገድ እንዲሳካ አበርክቶው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

ሸሙ በመላው ሀገሪቱ 15 ኢንዱስትሪዎች ያሉት ግዙፍ ተቋም እንደሆነ ጠቁመው፣ ለኢንዱስትሪዎቹ መስፋፋት የኤሌክትሪክ አቅርቦት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለግድቡ ግንባታ እስከ አሁን በሚሊየን ብር የሚገመት ቦንድ መግዛታቸውን የገለጹት አቶ ተስፋሚካኤል፣ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ዘንድሮ ለግድቡ የተዘጋጀውን ቦንድ በወር ደመወዛቸው ከገዙት የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች መካከል የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽንና የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን በአርአያነት ይጠቀሳሉ፡፡

የፖሊስ ኮሚሽን የለውጥ ስራዎችና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ እንደገለጹት፣ ግድቡ ዜጎች አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሰሩ የሚያደርግ የሀገራችን ትልቁ ፕሮጀክት ነው፡፡

ዜጎች ከድህነት ለሚላቀቁበትና እናቶችን ከዘመናት ጪስ መታጠን ለሚገላግለው ግድብ ገንዘብ ብቻ ሣይሆን ህይወት ለመስጠት የኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት ቃል መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት ወይዘሮ አበባ አለማየሁ ለሶስት ጊዜ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረው፣ በመኃል በግንባታ ሂደት በተፈጠረው መሰናክል ቦንድ የመግዛት ፍላጎታቸው መቀዝቀዙን አስታውሰዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ በአዲሱ የለውጥ አመራር ቁርጠኝነት ዳር ለማድረስ እየተከናወነ ያለው ተግባር እሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ዜጎች ያነቃቃ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

“ዘንድሮ ቦንድ ለመግዛት ወስኛለሁ፤ በሚቀጥለው ወር በልጆቼ ስም ለመግዛትም አቅጃለሁ” ሲሉም ያላቸውን ዝግጁነት ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ገበየሁ ወጋየሁ ዘንድሮ ለግድቡ ግንባታ 7 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታስቦ እስከአሁን 4 ሚሊየን ብር ከቦንድ ሽያጭ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የግድቡ መሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጀምሮ ከ87 ሚሊየን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ለግድቡ ድጋፍ መደረጉን ማስታወሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡