ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ዕጣ የማውጣት መርሀ-ግብር እየተካሄደ ነው

መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ድልድል ዕጣ የማውጣት መርሀ-ግብር እየተካሄደ ይገኛል።

ዕጣ የማውጣት መርሀ-ግብሩ በሀገራዊ ምርጫው የሚወዳዳሩ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን እና ፖሊሲያቸውን የሚያስተዋውቁበትን መገናኛ ብዙኃንና የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓት የጊዜ ሰሌዳ እንዲያውቁ የሚያስችላቸው እንደሆነም ተገልጿል።

57 የሚዲያ ተቋማት በዕጣው የተደለደሉ ሲሆን፣ የፓርቲ ተወካዮች እጣውን በማውጣት በሚዲያዎቹ የሚኖራቸውን አየር ሰዓት እየተከታተሉ ነው፡፡

በአየር ሰዓት ድልድል እጣ በማውጣት ሂደቱ በእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካይ የተከናወነ ሲሆን፣ በሂደቱም 46 የፖለቲካ ፓርቲዎች የአየር ሰዓት ድልድል ዕጣ መተግበሪያ ውስጥ ተመዝግበዋል ተብሏል።

ዕጣ በማውጣት መርሀ-ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና የመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን አመራሮችም ተገኝተዋል።

የምርጫ ቅስቀሳ የአየር ሰዓት ድልድሉ ፓርቲዎች ባቀረቡት የእጩዎች ብዛት፣ በሴት እጩዎች ብዛት እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች እጩዎች ብዛት መሆኑ ተጠቁሟል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በወጣው ዕጣ መሰረት የመገናኛ ብዙኃን የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ከመጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም መጠቀም ይችላሉም ተብሏል።

(በደረሰ አማረ)