ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት አስታወቀ።

ገቢው በ2012 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከተሰበሰበውም ገንዘብ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገጹት ባለፉት ስድስት ወራት ለግድቡ ግንባታ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራት ተከናውነዋል።

ከሕዝብ፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ከህዳሴው ግድብ ዋንጫ እንዲሁም ከሌሎች መንገዶች ገንዘቡ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 02 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል

ባለፈው በጀት ዓመት አጠቃላይ ለግንባታው የተሰባሰበው 747 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፈው ዓመት የተከናወነው የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት ገቢውን እንዳሳደገው የገለጹት አቶ ሃይሉ ቀደም ባሉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ በዓመት የሚሰባሰበው ከ100 ሚሊዮን ብር የማይበልጥ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የገለጹት አቶ ሃይሉ በቀጣይ የንቅናቄ መድረኮችን እንደሚካሄዱና የተጀመሩ ዝግጅቶችን እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የኮቪድ 19 ፕሮቶኮልን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሥዕል ዐውደ ርዕይና ሙዚቃዊ ቴያትር ለማካሄድ ታቅዷልም ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክርም ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ 78 በመቶ መድረሱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡