6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ምሰሶ ለመትከል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው – ኢዜማ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የዴሞክራሲ ምሰሶ ለመትከል ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገለፀ፡፡

ፓርቲው ለቀጣይ ሃገራዊ ምርጫ የስነ ምግባር መመሪያ ማዘጋጀቱን እና ምርጫው ነፃና ገለልተኛ መሆን በሚችልባቸው ነጥቦች ዙሪያ ለፓርቲው አባላት ስልጠና መስጠቱን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ፓርቲያቸው ለቀጣዩ ምርጫ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረው ኢዜማን ወክለው ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤት የሚቀርቡ እጩዎችን በመምረጥ ሂደት ላይ መሆናቸው ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው ለዜጎች ችግር እልባት የሚሰጡ ነጥቦች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አሳውቋል፡፡

ፍትሃዊነትንና ዴሞክራሲን የተላበሰ ምርጫን ማካሄድ ይረዳ ዘንድ ምርጫ ቦርድ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት እንዲወጣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ለምርጫው ስኬት ከጥላቻ እና ከወገንተኝነት የፀዳ ትክክለኛነትን የተላበሰ መረጃን እንዲያደርሱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ምርጫን ፍትሃዊ ብሎም ተአማኒ ለማድረግ መንግስት በቅድመ ምርጫ ሂደቶች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ያነሱት ደግሞ የኢዜማ የምርጫ ስትራቴጂና ማኔጅመንት ኮሚቴ ፅ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ከውሰር ኢድሪስ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ከመግለፅ እስከ ምርጫ ቅስቀሳ ያለው ጎዳና ነፃነት የነገሰበት ሊሆን እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የኢዜማ  ብሄራዊ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ተክሌ ፈለቀ በበኩላቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በቀጣዩ ምርጫ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የፍርድ ሂደቱን የተፋጠነ በማድረግ እኩል የሆነ መድረክ ማመቻቸት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ነፃና ገለልተኛ ብሎም ዴሞክራሲ የሰፈነበት ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የሆነ እድልን መስጠት ቀዳሚ ስራ ማድረግ ሲቻል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በዴሞክራሲም ይሁን በፍትሃዊነት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ካሄደቻቸው ምርጫዎች ፍፁም የተለየ መልክ የያዘ እንደሚሆን እምነት እንዳለው ኢዜማ አመላክቷል፡፡

(በሄብሮን ዋልታው)