6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እንዲሆን እየሰሩ መሆናቸውን ፓርቲዎች አስታወቁ

                      አቶ ሙሳ አደም
መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – መጪው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰለማዊ እንዲሆን እየሰሩ መሆናቸውን የአፋር ህዝብ ፓርቲ እና የቦሮ ዴሞኪራሲያዊ ፓርቲ አስታወቁ።
የፖሊሲ አማራጮችን ይዘን ወደ መራጩ ህዝብ በመቅረብ የህዝቡን ልብ መግዛት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ህዝብ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሙሳ አደም ፓርቲያቸው በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ተመዝግቦ በስፋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ህዝቡ ገብቶ የምረጡኝ ቅስቀሳ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የምረጡኝ ቅስቀሳቸው በዋናነት በፖሊሲ አማራጮች ላይ ያተኮረ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፓርቲያቸው ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲያልቅ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሙሳ፣ ግጭትን ከሚጭሩ አጀንዳዎች በመራቅ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ምርጫው ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን ከፓርቲው እና ከአፋር ህዝብ ምን ይጠበቃል፣ በምርጫ ወቅት መራጩና ደጋፊው ምን ማድረግ አለበት በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከአባላቶቻችን ጋር በዝርዝር መወያየታውን ገልጸው፣ ከመንግስትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናበን ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ አስካሁን ያለው ሂደት ጥሩ ነው ያሉት አቶ ሙሳ፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ዙሪያ አንዳንድ ክፍተቶች መኖራቸውን አመልክተዋል። ፓርቲያቸው ቀጣዩ የምርጫ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡

           የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አመንቴ ገሺ
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው፣ ፓርቲያቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀው፣ በአሁኑ ወቅት የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በክልሉ ያለው ሰላም አንፃራዊ ቢሆንም ምርጫው እስከ መጨረሻው ድረስ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ፓርቲያቸው እየሰራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ አመንቴ፣ ለምርጫው ሰለማዊነትና ስኬት ፓርቲያቸው የሚቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ፓርቲው በምረጡኝ ቅስቀሳው በፖሊሲ አማራጮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመው፣ ከዚህ ጎን ለጎን ለሁሉም መሰረት ስለሆነው ሰላም እና የሀገር አንድነት ሰፊ ጊዜና ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተንበታል፣ በቅንጅትም እየሰራን ነው ያሉት አቶ አመንቴ፣ ይህንንም እስከ መጨረሻው እንቀጥልበታለን ብለዋል።
ለሰላሙ ቀጣይነት እዛም እዚም ተከፋፍለን ህዝቡን ከማተራመስ የፖሊሲ አማራጮቻችንን ይዘን ወደ መራጩ ህዝብ በመቅረብ የህዝቡን ልብ መግዛት፣ ከዚህም በላይ በሀገር እና በህዝቦች አንድነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ለዚህም እውነት ተገዥ እንዲሆኑም ጥሪ ማቅረባቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡