ለአርቲስት አሊ ቢራ የምስጋና እና የእውቅና መርሃ ግብር ሊዘጋጅ ነው

ለክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ የምስጋና እና እውቅና መርሃ ግብር እንደሚካሄድ የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ ግብረሩ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አድናቂዎቹ እና የአርቲስቱ ወዳጆች በተገኙበት ይካሄዳል፡፡

መርሃግብሩም አርቲስቱ ከ60 ዓመታት በላይ ለኦሮሞ ኪነ-ጥበብ እድገት ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጨምረው ተናግረዋል።

በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም ተገልጿል።

በወቅታዊ ክስተቶች ሳይሸነፍ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት እንደሚያደርገውም አውስተዋል።

ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በሚካሄደው መርሃግብር የአርቲስቱ የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎች ላይ የተፃፈ መጽሐፍ እንደሚመረቅም ኃላፊው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የተመሰረተውን የመጀመሪያው የኦሮሚኛ ቋንቋ የኪነት-ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው።

አርቲስቱ ከኦሮሚኛ በተጨማሪ፣ በሱማሊኛ፣ በአፋርኛ፣ በሐረሪ፣ በአማርኛ እና በሱዳን ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።