መንግሥት በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ፈጽሟል-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ሰኔ 20/2015 (ዋልታ) በተለያዩ ክልሎች አርሶ አደሩ የሚያነሳውን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጥያቄ ምላሸ ለመስጠት መንግስት በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

መንግስት ለዓመቱ ገዥ እንዲፈጸም ካደረገው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ669 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ተጓጉዞ ካለፈው ዓመት ከተረፈው 210 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ጋር ተጨምሮ ከ879 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ማዳበሪያ አቅርቧል፡፡

ወደ አገር ውስጥ ከገባውና ከተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 842 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ለሕብረት ሥራ ማህበራት የተከፋፈለ ሲሆን ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርስ እየተደረገ ያለው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ደግሞ 706 ሺህ ሜትሪክ ቶን መኆኑን ጠቁሟል፡፡
አሁንም 172 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ በእጅ የሚገኝ ሲሆን ማዳበሪያው የሚፈለግበት የእርሻ ወቅት ሳያልፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ማዳበሪያውን በፍጥነት ለማድረስ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ጭነው ጅቡቱ ወደብ ከደረሱት 13 መርከቦች መካከል በ5 መርከቦች የተጫነው የአፈር ማዳበሪያ በቅርቡ መጓጓዝ ይጀምራል፡፡

የግብአት አቅርቦት በሚፈለገው ልክ አለመድረስ ደግሞ በቀጣዩ አመት ሃገራዊ ምርትና ምርታማነት ላይ የራሱን ተፅእኖ ስለሚያሳርፍ አርሶአደሩ በጊዜው የአፈር ማዳበሪያም ሆነ ሌሎች የግብርና አቅርቦቶች እንዲደርሱት ማድረግ በዚህ ዘርፍ ያሉ አካላት ቀዳሚ ሃላፊነት በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ ይገኛል።

በተጨማሪም በዘርፉ ብልሹ አሰራር ያለባቸውና ተገቢው ግብአት ለአርሶ አደሩ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆኑትን አካላት በተከታትሎ በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር በአንዳንድ ክልሎች ተጀምሯል። ይህ ተግባር በሁሉም ክልሎች የሚቀጥል ይሆናል።

የበልግ እርሻ እንቅስቃሴ ስራን በተመለከተ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፤ በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ እስከ ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡

በክላስተር የታረሰ መሬትን በሚመለከት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ክልሎች 4 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ በዘር መሸፈኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል።