የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

ሰኔ 22/2015 (ዋልታ) ከግጭት በኋላ መልሶ የማቋቋም ስራው ውጤታማ እንዲሆን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ 112 የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት የያዘ ልዑክ በቀጣይ ሳምንት ወደ አዲስ አበባ እንደምመጣ አስታውቀዋል።

ከድህረ ግጭት በኋላ መልሶ የመገንባት ስራውን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸው ገጽታ ግንባታ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የጅቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለቱሪዝም መነቃቃት ይፈጥራል ብለዋል።

በሌላ በኩል በሳምንቱ በአዲስ አበባ የተካሄደው የናይል ተፈሰስ ሀገራት ጉባኤ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተመዘገቡበት እንደነበር ገልጸዋል።

የተፋሰሱ ሀገራት በጋራ መልማት በሚችሉበት ሁኔታ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት መሆኑን አመልክተዋል።

የናይል ጉዳይ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እንደሚወሰደው ሁሉ ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት የመልማት ጉዳይ መሆኑ ላይ መግባባት ላይ ተደርሶበታል ተብሏል።

የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ፕሮጀክት ይዘው መስራት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል።

ባሳለፍነው ሳምንት ሰፋፊ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራዎች መሰራታቸውም ተጠቅሷል።

በመስከረም ቸርነት