ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ሰኔ 20/2015 (ዋልታ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለ1444ኛው ዒድ አል አድሃ አረፋ በዓል የአንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለ1444ኛው የዒድ አል አድሃ በዓል የተላለፈ መልእክት
ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወገኖቼ!
እንኳን ለታላቁ የዒድ አል አድሃ በዓል አደረሳችሁ!

ዒድ አል አድሃ፣አረፋ ሙስሊሞች በታላቅ ክብር እና ፍቅር የሚያከብሩት፣ መሥዋዕትነትን የሚዘክር በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች መካከል አንዱ የሆነውና ማንኛውም ሙስሊም የገንዘብና የጉልበት ዐቅሙ እስከፈቀደ ድረስ በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ ወደ መካ በመጓዝ እንዲያከናውነው የሚጠበቅበት የሐጅ ሥርዓት የሚካሄድበትና የሚጠቃለልበት ታላቅ ምዕራፍ ነው፡፡

አረፋ፣ የሰው ልጅ ለፈጣሪው እና ለእምነቱ ሲል፣ መከራ ለመቀበል፣ ካስፈለገም ለመሠዋት ያለውን ፈቃደኛነት የምናስታውስበት፣ የምናከብርበት፣ የምንዘክርበት ልዩ ቀን ነው፡፡ አላህ (ሱብሀነሁ ወተአላ)፣ ነቢዩ ኢብራሂምን፣ ልጅህን መሥዋዕት አድርግልኝ ብሎ ሲያዛቸው፣ ነቢዩ ኢብራሂም፣ የአባት ኀዘን አላሸነፋቸውም፤ የልጅ ፍቅር አላጓጓቸውም፣ የቤታቸው መፍረስ አላሳሰባቸውም፤ የትኛውም ጉዳይ ከፈጣሪ ትእዛዝ አይበልጥምና፣ አንድዬ ልጃቸውን እስማኤልን መሥዋዕት ለማድረግ ተነሡ፡፡ ልጃቸው እስማኤልም ለመሠዋት ዝግጁ ነበር፡፡ ዒድ አል አድሃ የመሥዋዕት በዓል ነው የሚባለውም ለዚያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያውያን፣ ከዚህ ጥንታዊ ኢስላማዊ ታሪክ ሁለት ታላላቅ ቁም ነገሮችን ተምረናል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ፣ ሰዎችም በአስቸጋሪ ጊዜዎች ይፈተናሉ፡፡ እንደ እስማኤል ያለውን ነገር ሁሉ ሰጥቶ ለመሠዋት የቆረጠ ፈተናውን አልፎ፣ ትልቅ ታሪክ ጽፎ፣ እንደ ዒድ አል አድሃ ያለውን መታሰቢያ አትርፎ፣ ከዘመን ዘመን እየታወሰ ይኖራል፡፡ መሥዋዕትነትን ያልደፈረ፣ ከክብር ርቆ፣ ከታሪክ ተፍቆ እንደ አቧራ ይበናል፡፡

ሁለተኛው ትምህርት፣ ታላቅ ግብ ላይ የሚደረሰው የሚወዱትን እንኳን ሳይቀር አሳልፎ በመስጠት መሆኑን ነው፡፡ ነቢዩ ኢብራሂም ለእስማኤል የማይለካ ፍቅር ነበራቸው፡፡ ትልቁ ግባቸው ግን የፈጣሪያቸውን የአላህን ፈቃድ መፈጸም ነው፡፡ ይሄንን ግባቸውን ለማሳካት ሲሉ በምድር ላይ ትልቁ ሀብታቸው አድርገው የሚቆጥሩትን እስማኤልን ለመሠዋት ቆረጡ፡፡

የመሥዋዕትነት በዓል በሚከበርበት በዚህ ልዩ ቀን፣ ኢትዮጵያውያን ‹እንኳን አደረሳችሁ› እንዲባባሉ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱንም ቁም ነገሮች ልብ እንዲሉ አደራ እላለሁ፡፡ ለትልቅ ጉዳይ መፈተን፣ ለብርቱ ጉዳይ መሥዋዕት ለመሆን መዘጋጀት ታላላቅ ሰዎች የሚፈጽሙትና ታሪክ የሠሩበት ዕሴት ነው፡፡ ለታላቅ ግብ ሲባል የሚወዱትን ሳይቀር ለመሠዋት መቁረጥም ዓለምን የሚለውጥ ታሪክ የሚሠሩ ሁሉ የሚፈጽሙት ነው፡፡

ሀገራችን፣ በተለያዩ ጊዜዎች የተለያዩ ችግሮች ገጥመዋት ያውቃሉ፡፡ የሚታለፉ የማይመስሉ ፈተናዎች በየወቅቱ ቢደቀኑባትም፣ ችግሮቹንና ፈተናዎቹን ተራ በተራ አልፋ፣ ወደ ፊት በመጓዝ ላይ ነች፡፡ መከራው በበዛ ጊዜም፣ ዜጎቿ የመጨረሻውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ወደ ኋላ አላሉም፡፡ ንብረታቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወታቸውን ለመስጠት አላቅማሙም፡፡ ኢትዮጵያን እዚህ ያደረሷት፣ ልጆቻቸውን ጭምር የከፈሉ ልጆቿ መሆናቸውን ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ደማቅ ታሪካችን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውንም መሥዋዕት ያደርጋሉ፡፡ የሚወዱትንም ነገር ለሀገራቸው ሲሉ ይሠዋሉ፡፡

ዛሬ፣ በታላቁ የመሥዋዕትነት በዓል ላይ ቆመን፣ ሁለቱንም በክብር እናስታውሳለን፡፡
በድጋሚ፣ እንኳን ለዒድ አል አድሃ/ አረፋ በዓል አደረሳችሁ!

ያለ መሥዋዕትነት የጸና ሀገር፣ የበለጸገ ሕዝብ በዓለም ላይ የለም፡፡ ዓለም የተራመደችበት የዕድገት ደረጃ ሁሉ የመሥዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ አሁን የደረስንበት ደረጃ ላይ እንድንደርስ ብዙ ወገኖች ራሳቸውንም የሚወዱትንም ነገር መሥዋዕት አድርገዋል፡፡ ከመኖር ለሚበልጥ ግብ ሲሉ ሕይወትን ያህል ውድ ነገር ከፍለዋል፡፡ ሀገር ሀገር የምትሆነው ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ከፍም ሲል ሕይወታቸውን ለመሥዋዕትነት የሚያቀርቡ ብዙ ልጆች ማፍራት ስትችል ነው፡፡ አንዱ ለሌላው መሞት፤ አንዱ ለሌላው መስጠት፤ አንዱ ለሌላው ማካፈል፤ አንዱ ለሌላው ሲል መሥዋዕትነትን መክፈል ነው የዓለምን ሥልጣኔ በጽኑ መሠረት ላይ ያቆመው፡፡

ጥላቻ፣ ግጭት፣ መከፋፈልና መገፋፋት መሥዋዕትነት ባለበት ቦታ አይኖሩም፡፡ እነዚህ የስግብግብነት ውጤቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ታላቅ በመሥዋዕትነት የተሞላ ፍቅር በሚከበርበት በዓል፣ የትም ይሁን የት፣ ጥላቻን መስበክ ሐራም ነው፡፡ መለያየትንና መገፋፋትን መስበክ ነውር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ አሁን የምትፈልገው ፍቅርን እና የሕዝቦቿን አንድነት ነው፡፡

አደምና ሐዋ ከገነት ከተባረሩ በኋላ በተገናኙበት የአረፋ ኮረብታ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሙስሊሞች የዒድ አል አድሃን በዓል በአንድነት ያከብራሉ፡፡ ምንጫቸው የተለያየ፣ ቀለማቸው የተለያየ፣ ዜግነታቸው የተለያየ፣ ማንነታቸው የተለያየ ቢሆንም፣ ሁሉም የሚያስቡት ሙስሊም መሆናቸውን ብቻ ነው፡፡ የተለያዩበትን ረስተው የተገናኙበትን፣ የተሣሠሩበትን እያሰቡ፣ አንድ ይሆናሉ፡፡ እኛም ለምንለያይበትን ሳይሆን ለምንገናኝበት፣ ለምንገፋፋበት ሳይሆን ለምንሳሳብበት፣ ለምንሻኮትበት ሳይሆን ለምንተባበርበት ቅድሚያ ሰጥተን፣ አንድ ትልቅ ሕዝብ እንሁን፡፡ ከልዩ ልዩ ቦታ ብንመጣም፣ ልዩ ልዩ ማንነት ቢኖረንም፣ የተለያየ ቋንቋ ብንናገርም፣ የተለያየ ሃይማኖት ብንከተልም፣ ኢትዮጵያ ሲባል አንድ እንሁን፡፡

ይህ መንደር ይህ ሠፈር የእኔ ነው ማለትን ትተው፣ ኢትዮጵያ የእኛ ናት የምንል ዜጎች እንድንሆን አደራ እላለሁ፡፡ ሁሉንም አካባቢ ለሁላችንም እንዲበቃ አድርገን ልናለማው፣ ልናበለጽገው እንችላለን፡፡ ከነካነው ያልነካነው ሀብታችን ይበልጣል፤ ከሠራነው ያልሠራነው ይበዛል፡፡

ልጆቿ ተደማምጠው እና ተከባብረው፣ በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩባትን ሀገር፣ በጋራ እንድንገነባ ሙስሊሞችን ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉንም እምነት ተከታዮች በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከምንም ነገር በላይ ዛሬ የምትፈልገው፣ መከባበርን እና መፋቀርን ነው፡፡ አንዳችን ሌላችንን እንድንሠዋ ሳይሆን፣ አንዳችን ለሌላችን ብለን እንድንሠዋ ነው፡፡ አንዳችን የሌላውን ሞት እንድንሞት ነው፡፡ ከዘመናት በፊት ነቢዩ ኢብራሂም ስለ እምነታቸው እንደተፈተኑት ሁሉ፣ እኛም ዛሬ ስለ ሀገራችን ስንል በፈተና ላይ ነን፡፡ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ከድህነት ለመውጣት፣ ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ፣ ሕዝባችንን ለማበልጸግ ትግል ላይ ነን፡፡ ተጋጭተን ሳይሆን ተነጋግረን፤ ተሻምተን ሳይሆን ተካፍለን፤ ተገፋፍተን ሳይሆን ተጋግዘን፤ ለሀገራችን ከሠራን፣ ፈተናችንን ያለምንም ጥርጥር በድል እንወጣዋለን፡፡ እኛ ተሠዉተን ኢትዮጵያን እናጸናለን፡፡ የነቢዩ ኢብራሂም ታሪክ ለትውልድ ሁሉ ተርፎ ሚሊዮኖችን ከመላው ዓለም ወደ አረፋ ተራራ እንደሚስበው ሁሉ፣ የእኛም ታሪክ ለትውልድ ተርፎ ሚሊዮኖችን ከመላው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚስባቸው አምናለሁ፡፡

ዒድ ሙባረክ!
መልካም የዒድ አል አድሃ በዓል!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም