መጥፎ የእግር ጠረን መንስኤና መፍትሄዎች


ጠረን ማህበራዊ ግንኙነታችንን በበጎም ይሁን በአሉታዊ መልኩ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ መልካም ጠረንና መዓዛ ያላቸው ሰዎች ሳቢና ጥሩ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ሌሎች ሰዎች በቅርባቸው ለመሆን ይሻሉ፡፡

በተቃራኒው መልም ያልሆነ ጠረን ደግሞ ማህበራዊ መስተጋብሩን ችግር ውስጥ ይከተዋል፡፡ የእግር የብብት ወይም የአፍ ወይም ሌላ የሰውነት ክፍል ጥሩ ያልሆነ ጠረን ከፈጠረ ሰዎች ሊሸሹ ይችላሉ፡፡ ተቀራርቦ ለማውራትም ይሁን ለመስራት ሊቸገሩ ይችላሉና፡፡

የእግር ሽታ አንዱና ዋነኛው የብዙ ሰዎች ችግር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመሆኑም የእግር ጥሩ ያልሆነ ጠረን መንስኤዎች አባባሽ ሁኔታዎችንና በቤታችን ልንወስዳቸው የምንችላቸውን የመፍትሄ እርምጃዎችን እንዳስሳለን፡፡

የእግር መጥፎ ጠረን መንስኤዎች

እግራችን መጥፎ ጠረን ሊኖረው የሚችለው በሙቀት ምክንያት እግራችን የሚያመነጨው ላብና ላቡን እየተመገቡ በሚያድጉ ባክቴሪያና ፈንገስ መራባት ምክንያት ነው፡፡

በተለይ የምንጫማው ጫማ ሽፍን ከሆነ በእንቅስቃሴ ወቅት ሙቀት እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ሙቀት ደግሞ እግር ላብ እንዲያልበው ያደርጋል፡፡ ባክቴሪያና ፈንገስ ለማደግ እርጥበት ጨለማና ሙቀት ይወዳሉ፡፡ ጫማ ደግሞ ሶቱስንም ነገሮች ያሟላ አመቺ የመራቢያ ቦታ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለሆነም ሽፍን ጫማ ሙቀትና ላብ ተደማምረው እግራችን ጠረን እንዲፈጥር ያደርገዋል፡፡ ፈንገስና ባክቴሪያዎች ደግሞ ላባችንን እየተመገቡ ለመራባትና ለመባዛት አመች ሁኔታዎች ይፈጥርላቸዋል፡፡

የእግር ጠረን እንዲፈጠር የሚያባብሱ ሁኔታዎች

• የሚሞቅና ናይለን የሆኑ የእግር ሹራብ መጠቀም
• እግርን በየቀኑ በሚገባ አለመታጠብ
• ንጹህ ጫማ አለመጫማትና በተወሰነ ጊዜ አለመቀያየር
• ንጹህ የእግር ሹራብ አለማድረግና ቶሎ ቶሎ አለመቀየር
• ሞቃታማ አየር ንብረት
• ከባድና እንቅስቃሴ የበዛበት ስራ መስራት
• በየቀኑ ረጅም የእግር ጉዞ ማድረግ
• የእግር ቁስለት
• የእግር ጥፍር በፈንገስና በባክቴሪያ መጠቃት
• እግርን ሳያደርቁ ጫማ መጫማት
• ጫማንና የእግር ሹራብን ሳያደርቁ መልበስ ወዘተ ናቸው፡፡

በቤት ውስጥ ልንወስዳቸው የምንችላቸው ቀላል የመፍትሄ እርምጃዎች

1. ኮምጣጤ – የኩባያ አንድ ሶተኛ ኮምጣጤ ፈሳሽ በሞቀ ወይም በቀዝቃዛ ውሃ በተሞላ ሳፋ ውስጥ እግርን መዘፍዘፍ። በሆምጣጤ ውስጥ ያለው አሲድ የእግርን መጥፎ ጠረን ከማስወገዱም በላይ ባክቴሪያዎችን ለማጥፋት ይረዳል፡፡

2. አልኮል – እግርን በደንብ መታጠብ እና ማድረቅ ቀጥሎም የተወሰነ አልኮልን ውስጠኛው እግር (በጣቶቻችን ስር) ላይ በማፍሰስ ማዳረስ እና ማሸት በደንብ ሲደርቅም እግርን አናፍሶ ከደቂቃዎች በኋላ ጫማ ማድረግ።

3. ሽንኩርት – አነስ ያሉ አራት ራስ ሽንኩርቶችን ልጦ በስሱ መጨቅጨቅ ቀጥሎም በደንብ ታጥቦ የፀዳው እግርዎ ላይ በጨርቅ በማድረግ ማሰር እና ከሶስት ሰአታት በኋላ በመፍታት ማናፈስ ለእግር ጠረን ጥሩ መፍትሄ ነው።

4. ጨው – ለብ ባለ ውሃ ውስጥ ጨው በመነስነስና እግርን ጨው በተጨመረው ውሃ መዝፍዘፍ ሌላው መፍትሄ ነው፡፡ አጠቃቀሙ አንድ ተኩል የሾርባ ማንኪያ ጨውን በአንድ ጆግ ውሃ በማፍላት ቀዝቀዝ አድርጎ እግርን ለ20 ደቂቃ መዝፈዝፍ ሲሆን ለሁለት ሳምንታት ያህል በየቀኑ መደጋገም ይመከራል ።

5. የሻይ ቅጠል – ሁለት የሚነከሩ የሻይ ቅጠሎችን ወይም ተመጣጣኝ መጠን ያለውን ብትን የሻይ ቅጠል በሶስት ብርጭቆ ውሃ ማፍላት እና ከፈላ በኋላ በግማሽ ባልዲ ውሃ መቀላቀል፡፡ ውሃው ለብ ሲል እግርን ከ15 እስከ 20 ደቂቃዎች ዘፍዝፎ ማቆየት እና ለሳምንት ያህል ይህን መደጋገም። በተለይ ጥቁር ሻይ ታኒክ የተባለ ባክቴርያዎችን የሚገድል አሲድ ስላለው የእግርን ጠረን ለማጥፋት ያግዛል፡፡

6. ቤኪንግ ሶዳ – አንድ የሾርባ ማንኪያን ቤኪንግ ሶዳ በእጅ ማስታጠቢያ ግማሽ ለብ ያለ ውሃ መቀላቀል እና እግርን እስከ 20 ደቂቃዎች ድረስ መዘፍዘፍ ከዛም እግርን ማድረቅ ይገባል፡፡ ይህንን በተከታታይ ለአንድ ሳምንት ማድረግ ይጠበቃል።

7. እግራችን ጠረን እንዲኖረው የሚያደረጉትን አባባሽ ሁኔታዎችን በመለየት ማስወገድ ሌላው መፍትሄ ነው፡፡

(በቴዎድሮስ ሳህለ)

ምንጭ፡ Reader’s Digest Canada
Cleveland Clinic
National Health Service (N H S UK)