ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የፖን አፍሪካኒዝም እሳቤ እንዲሰርጽ በትኩረት ይሰራል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

ነሐሴ 11/2015 (አዲስ ዋልታ)- ከጎረቤት አገራት ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የቀጣናውን ሰላም የማስከበርና የፖን አፍሪካኒዝም እሳቤ ማስረጽ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እንደሚሰራባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ ሶስት አመታት የመንግስት የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ዝግጅት ላይ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።

 

በውይይቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴርና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ሁሉንም ዓይነት የዲፕሎማሲ መንገዶች መጠቀሟን ገልጸው

በባለብዙ ወገን የግንኙነት ማዕቀፎች ያላትን ተሳትፎ የበለጠ ለማሳደግና ዘላቂ ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

 

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የዳያስፖራው ሚናና ተሳትፎ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

በውይይቱ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማሳደግ፣ የኢትዮጵያን አቋም በመገንዘብ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን የማስገኘት፣ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የኢትዮጵያን ገጽታ የማሳደግ እና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አቅምን በማጎልበት የውጭ ሀብት ፍሰትን ማሳደግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

 

የዜጎች መብት ማስከበርና የዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ሁለንተናዊ ተሳትፎ የማጎልበትና የማሳደግ፣ የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ እንዲጎለብት በ2015 በጀት ዓመት የተከናወኑ ስራዎች ላይ እና በ2016 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ምክክር መደረጉም ተገልጿል።

 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)  በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።