መጪውን አገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መንግስት እየሰራ ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – መጪውን አገራዊ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መንግስት በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአገሪቷ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ምርጫውን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው አሳስበው፣ መንግስት ከግማሽ መንገድ በላይ ሄዶ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ጥረት ማድጉን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማካሄድ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያ መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉም ዛሬ በተካሄደው 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ አመላክተዋል።
በምርጫው ያልተሳተፉ ፓርቲዎች በምርጫው እንዲሳተፉ በመንግስት በኩል ጥረት መደረጉን የጠቀሱት ዶክተር ዐቢይ፣ በግል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲን በምርጫው እንዲሳተፍ ማነጋገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሽማግሌዎች ባሉበት ጥያቄ የቀረበላቸው ፓርቲዎች መኖራቸው እንደሚታወቅና ምርጫ ማጀብ የለመዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረው ለማሸነፍ እንደማይፈልጉ አንስተዋል።
ምርጫ ዲሞክራሲ እንዲፈጠር ዋና መሰረት ነው፤ በአንድ ምሽት የሚፈጠር ዲሞክራሲ የለም፤ ዲሞክራሲ በአንድ ምርጫ የሚመለስ ሳይሆን በሂደት የሚፈጠር መሆኑንም አብራርተዋል።
ብልፅግና ከመቶ ሺህ በላይ ካድሬዎችን “የእኛ ድል ምርጫውን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ነው” በሚል ይህን አቋም እንዲይዙ ስልጠና መስጠቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የለመዱት ምርጫ ማጀብ እንጂ ማሸነፍን አይደለም፤ ይህን ባህል ለመቀየር እየሰራን ነው ሲሉም አክለዋል።
አሁን ከማንኛውም ወቅት የተሻለ ምርጫ ለማድረግ አመቺ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ ፓርቲያቸው ከተሸነፈ ወንበሩን እንደሚያስረክብ ደጋግሞ ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል፡፡
(በአድማሱ አራጋው)