መጪው ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ዋጋ የሚያገኝበት እንዲሆን ኃላፊነታችንን እንወጣላን – የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች

መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – በመጪው ምርጫ የሕዝብ ድምጽ ካለፉት ምርጫዎች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ።
አገራዊውን ምርጫ ለመታዘብ 155 ገደማ አገር በቀል የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ፈቃድ ወስደዋል።
ከእነዚህም የኢትዮጵያ ወጣቶች ሠላምና ብልጽግና ተልዕኮ ሊግ ለመራጮች ትምህርት ለመስጠትና ምርጫውን ለመታዘብ ፈቃድ አግኝቶ በዝግጅት ላይ መሆኑን የሊጉ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ በቀለ ገልጸዋል።
እስካሁንም በአዲስ አበባ ለወጣቶች፣ ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች ከምርጫ ጋር የተያያዘ ስልጠና መስጠቱን ገልጸው፣ በዚህም ከመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 1 ሺህ 500 ወጣቶችና ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች መካተታቸውን ጠቅሰዋል።
የምርጫውን ሂደት ፍትሃዊነት ለመታዘብ 101 ወጣቶችን በመላ ሀገሪቷ ለማሰማራት መታቀዱንም ነው የገለጹት።
የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ ፈቃድ ያገኘው ሌላው አገር በቀል ድርጅት ‘ፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ’ ሲሆን፣ የድርጅቱ ኃላፊና የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ለምርጫው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
መጪው ምርጫ በአይነቱ ልዩና መሸጋገሪያም እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ማደሩን የገለጹት አቶ አህመድ፣ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ለውጤት እንዲበቃ ሂደቱን በቀናነት መታዘብ ይገባል ብለዋል።
ይህን ለማሳካት የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ የሁሉም አካላት ድርሻ ትልቅ በመሆኑ የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ከትግራይ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከጋምቤላ ክልሎች ውጭ በመላ አገሪቷ ከ200 እስከ 300 በሚደርሱ ወጣቶች ምርጫውን ለመታዘብ ያቀደው ደግሞ ‘ቼንጅ ፎር ኢትዮጵያ’ የተባለው ድርጅት ሲሆን፣ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፉአድ ጀማል በበኩላቸው፣ ለታዛቢነት የተዘጋጁት ግለሰቦች ምርጫውን ነጻ ሆነው እንዲመለከቱ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።
“ምርጫ ነገ ትልቅ ነገር ይዞ የሚመጣ ነው፤ ምክንያቱም ነገ መንግሥት የምናስቀምጥበት በመሆኑ ከየትኛውም ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ መታዘብ ይገባል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በመጪው ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።