ሰኔ 19/2013 (ዋልታ) – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለኮቪድ-19 ህሙማን የሚውሉ 20 ሺህ የቀርከሃ አልጋዎችን ለጤና ሚኒስቴር ድጋፍ አድርጓል፡፡
የቀርከሃ አልጋዎቹ ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት( ጂ አይ ዜድ) በተገኘ ድጋፍ የተሰሩ ናቸው፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኮሮና ቫይረስን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት የኢትዮጵያ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ጂ አይ ዜድ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፐን አውር በበኩላቸው የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳሃረላ አቡዱላሂም ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከጀርመን ተራድኦ ድርጅት ጋር በመተባበር ላከናወነው ተግባር ምስጋና እና እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ድጋፉ የኮቪድ-19 ህሙማን ወደ ህክምና ሲገቡ ሊከሰት የሚችለውን የአልጋ እጥረት ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መገለጹን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡