ማህበረሰቡ ክብረ በዓላትን ሲያከብር ቫይረሱን ሊከላከል ይገባል

ማህበረሰቡ በእምነት ተቋማት ሲገኝ እና ክብረ በዓላት ሲያከብር ራሱን ከኮሮናቫይረስ እየጠበቀ መሆን እንዳለበት ተገለጸ፡፡

በኮቪድ-19 ዙሪያ እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋት እና የቫይረሱን መስፋፋት በተመለከተ የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት እና ጤና ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸው ምዕመኑ በአምልኮ ስነ- ስርዓቶች እና በሃይማኖት ጉባኤዎች ላይ ሲገኝ ርቀትን በመጠበቅ፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብሎጭን በማድረግ እና ሌሎች መከላከያ መንገዶችን በመጠቀም ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መጪው ወር እንደ ገና፣ ጥምቀት እና ሌሎች ክብር በዓላቶች የሚከበሩበት በመሆኑ ማህበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሃገሪቱ የጭንብል አጠቃቀም ከ70 በመቶ ወደ 50 በመቶ መቀነሱን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ዴታዋ ወ/ሮ ሳህረላ አብዱላሂ ማህበረሰቡ እንደ ሰርግ፣ ክብረ በዓላትና እና ሌሎች ዝግጅቶች በሚከውኑበት ወቅት ቫይረሱን እየተከላከሉ መሆን እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

ሚኒስትር ዴታዋ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የጽኑ ህሙማን የመተንፈሻ እጥረት እያጋጠመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

(በሀኒ አበበ)