ምሁራን ከመተቸት ባለፈ ወቅታዊ ችግሮችን በመፈተሽ መፍትሔ ሊያቀርቡ እንደሚገባ ተጠቆመ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በማኅበራዊ ሚዲያ ከመተቸት ባለፈ ወቅታያዊ ችግሮችን በመፈተሽ የተደራጀ የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ሊያግዙ እንደሚገባ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እሰይ ከበደ (ዶ/ር) ገለፁ።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ዓመታዊ ኮንፈረንስ “ግጭት በኢትዮጵያ ከ2018 ጀምሮ” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ መሆኑን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሀገራዊ የምክክር መድረኩ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ እንዲኖረውና እንደ ዜጋ ንቁ ተሳትፊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ መድረኮችን በመፍጠር የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ እየሰራ ነው ብለዋል።

ምሁራን እንደ ሀገር እየተፈጠሩ ላሉ ችግሮች የተደራጀ የመፍትሔ ሃሳብ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸው ይህን ለማሻሻል መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አክለውም ከትችትና ተገቢ ያልሆነ ወገናዊነት የተጠናወተውና አለፍ ሲልም ሥነ-ምግባርን የሚተላለፍ ሃሳብ ከመሰንዘር ባሻገር ያሉ ችግሮችን በመፈተሽ የተደራጀ መፍትሔ አቅራቢ መሆን ይገባል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መስፍን (ዶ/ር) ሀገራዊ የምክክር መድረኩ መሰረታዊ የሆኑ መግባባቶችን እንዲፈጥር ታስቦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በብዙ መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ግጭት አፈታት ላይ እንደሚያተኩር ተድርጎ እንደሚገለጽ ጠቅሰው ነገር ግን ብሔራዊ የምክክር መድረኩ ግጭት መፍታት ላይ ሳይሆን መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ይሰራልም ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የዩኒቨርስቲው የቦርድ አባል ድረስ ሣህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአማራ ክልል ተለዋዋጭ ግጭት የሚበዛበት ክልል በመሆኑ ምሁራን ችግሩን በሚገባ በማጥናት ለቀጣይ የመፍትሄ አካል በማመንጨት ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።