የጽንፈኝነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል ተባለ

ግንቦት 15/2014 (ዋልታ) የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርን፣ ሃይማኖትን፣ ወሰንንና ሌሎች ማንነቶችን ሽፋን በማድረግ የተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ናቸው ብለዋል።

በሕዝብ ግፊትና ጫና የመጣውን ለውጥ መቀበል የተሳናቸው አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ ግጭቶችን ሲጠነስሱ፣ በገንዘብ ሲደግፉና ለጥፋት የመለመሏቸውን ኃይሎች ሲሰማሩ እንደነበረም አንስተዋል።

ጸረ ለውጥ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያለአግባብ ያጋበሱትን ሀብት መልሶ ለማግኘትና ስልጣንን ዳግም ለመቆጣጠር ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታልም ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ሲዘራ የነበረውን የጥላቻና በጥርጣሬ የመተያየት ትርክት ለግጭት መፍጠሪያነት ማዋላቸውንም ነው የገለጹት።

የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰሙ ግጭቶቹ እንዲባበሱ ካደረጉ ክስተቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን ገልጸው ለውጡን ማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት አዝማሚያውን ለግጭት መፍጠሪያና ማባባሻነት ተጠቅመውበታል ብለዋል።

ግጭት ጠማቂዎቹ የሀገር ውስጥ ጸረ ለውጥ ኃይሎች ብቻ አለመሆናቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያን መፍረስ የሚፈልጉ የውጪ ኃይሎች ተሳትፎም ነበረበት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በራሷ አቅም የማትፈታ ደካማ ሀገር እንድትሆን ቀን ከሌሊት ሲሰሩ የነበሩ የውጭ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያላት የጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ የማያስደስታቸው አካላት እንዳሉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።