ምክር ቤቱ በተለያዩ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ውሳኔ አሳለፈ

ግንቦት 30/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር እንዲሁም ስልጣንና ተግባሩን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ 251/1993 ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ ተጨማሪ የማሻሻያ ሀሳብ በማከል ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የማቋቋሚያ አዋጅ 556/2000ን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት ስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 1/1999ን ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ በጥልቀት ከተወያየና አስፈላጊነቱን ከመረመረ በኋላ አዋጁን በሙሉ ድምፅ ወስኗል።

ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ እንዳመላከተው በሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ተብለው በቀረቡለት 50 ጉዳዮች ላይ “የሕገ መንግሥት ትርጉም አያስፈልጋቸውም” በማለት ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን በሌሎች 14 ጉዳዮች ላይ ግን “የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል” በማለት ውሳኔ ተላልፏል፡፡