ጠ/ሚ ቦሪስ ጆንሰን ክትባቱ በመላው ዓለም እንዲዳረስ ኃያላን አገራት ላይ ጫና ሊያደርጉ ነው ተባለ

                                            ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን

ግንቦት 30/2013 (ዋልታ) – የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እስከ ቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት መጨረሻ ድረስ በመላው ዓለም የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንዲዳረስ ጫና ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተገለጸ።

በመጪው አርብ በአገራቸው በሚደረገው የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይህንን እቅዳቸውን ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።

አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ጃፓን ለዓለም አቀፉ የፍትሃዊ የክትባት ማከፋፈያ ፕሮግራም ኮቫክስ ምን ያህል ክትባት እንደሚያጋሩ ይፋ አድርገዋል። እንግሊዝ እና ካናዳ ግን ምን ያህል አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ እስካሁን ይፋ አላደረጉም ነው የተባለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሮና ቫይረስ ጋር እየተደረገ ያለውን ፍልሚያ በስኬት ለማጠናቀቅ እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ በመላው ዓለም ክትባቱን ለማዳረስ ለመሪዎቹ በኮርንዌሉ ጉባኤ ላይ ጥሪ ያቀርባሉ።

እንዲህ ዓይነቱ ስኬት ‹‹በሕክምና ታሪክ ውስጥ ብቸኛና ታላቁ›› ይሆናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ።

አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን የማምረት ምጣኔን እንዴት ከፍ ማድረግ እንደሚቻል የሚደረጉ ውይይቶችን እንደምታበረታታም ተገልጿል።

የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ከወረርሽኙ መከሰት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ገፅ ለገፅ የሚደረግ ሲሆን፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ወደ እንግሊዝ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ይሆናል ተብሏል።

እንግሊዝ ምን ያህል ክትባት ለኮቫክስ እንደምታበረክት በጉባኤው ላይ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት የፓርላማ አባላት ብሎም የአገራት መሪዎች እንግሊዝ የተያዘው የፈረንጆች ዓመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቢያንስ 100 ሚሊየን ክትባት እንድታበረክት ደብዳቤዎችን እንደፃፉላቸው ይታወሳል።

የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በበኩላቸው፣ ‹‹እውነታው›› መንግስታት ‹‹የራሳቸውን ሰዎች የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው››፤ ሁል ጊዜም ለራሳቸው ዜጎች ክትባት ቅድሚያ ይሰጣሉ ሲሉ መናገራቸውን አስታውሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አክለውም በዚህ ጉዳይ ፍፁም መሆን አይቻልም፤ ከመዳረሱ በፊትም የተወሰነ ክትባት መለግስ ይቻላልም ብለዋል።