ምክር ቤቱ የቀረበውን ተጨማሪ 616 ሚሊየን ብር በጀት አጸደቀ

የደቡብ ክልል  ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዙር፣ 6ኛ አመት የስራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ጉባኤው በቀረበለት የተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት 616 ሚሊየን 843ሺህ 300 ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ቀጣዩን ምርጫ በሚመለከት የተወካዮችን ብዛት የሚወስን አዋጅን ማጽደቁ ተገልጿል።

ከጸደቀው በጀት ውስጥ 350 ሚሊየን በገንዘብ እጥረት ምክንያት በበጀት ላልተደገፉ ልዩ ልዩ ፕሮጅክቶችና ለሌሎች ተግባራት፣ 156 ነጥብ 7 ሚሊየን ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ለክልሉ ጤና ቢሮ፣ 10 ነጥብ 1 ሚሊየን ለትራንስፖርት ቢሮ ለነባር የዩራፕ መንገድ ፕሮጀክቶች እና 100 ሚሊየን ለክልሉ መጠባበቂያ በጀት የሚውል ነው ተብሏል።

የምክር ቤቱ አባላት ተጨማሪ በጀቱ እንደ ውሃ፣ መንገድና ጤና ባሉ የህብረተሰብ ፍላጎቶች እንዲሁም በአዳዲስ የወረዳና የዞን መዋቅሮች ድጋፍ ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በጀትን በግልጽነትና በፍትሃዊነት ለመደልደል እንዲሁም ውጤታማ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ጥረት መደረጉን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡