ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ

መጋቢት 21/2015 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ አዋጅን አስመልክቶ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፀደቀ።

የውሳኔ ሃሳቡን ያቀረቡት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ሁሉን አቀፍ፣ ወጥና አስተማማኝ የሀገሪቷ ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት ሥርዓት በመዘርጋት እና የተመዝጋቢዎችን መረጃ በመያዝ የዲጂታል መታወቂያ አጠቃቀም ሥርዓትን ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

መታወቂያውን በመጠቀም በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ የግልፅነትና ተጠያቂነት አሰራር ሥርዓት እንዲዘረጋና የተሳለጠ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት እንዲኖር አመቺ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

አዋጁ ረዘም ላለ ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ሰብሳቢዋ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት የተጭበረበረ መታወቂያ ሰጥተው ከተገኙ ከበድ ያለ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እና አስተማማኝነቱም በመርህ ላይ መመስረቱን አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ በጉዳዩ ዙሪያ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል።