በአንድ ዓመት ውስጥ 125 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አረቢያ መመለሳቸው ተገለጸ

አምባሳደር መለሰ አለም

መጋቢት 21/2015 (ዋልታ) በአንድ ዓመት ውስጥ 125 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ አረቢያ መመለሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ በውጭ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያድረግ ስራ ከተጀመረ አንድ ዓመት እንደሞላው ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተደረገ የቅንጅት ስራ ከሳውዲ አረቢያ ብቻ 125 ሺሕ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

አምባሳደር መለሰ አለም ከሳውዲ አረቢያ በተጨማሪ ከምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

በሳምንቱ የተከናወነውን ዲፕሎማቲክ ሁነቶችን በተመለከተም ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደር መለስ በሳምንቱ ጠንካራ የሚባል ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት መከናወኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰራ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ለዚህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ከሰላም ጋር አስተሳስሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የመሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ከማድረግ ጀምሮ ህወሓትን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአሸባሪነት መሰረዙ ትልቅ እርምጃ ነው ተብሏል።

በመስከረም ቸርነት