የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገልን መልካም አቀባበል ከችግርና ሞት ታድጎናል – ሱዳናዊያን ስደተኞች

ሐምሌ 2/2015 (ዋልታ) “የኢትዮጵያ መንግሥት ድንበሩን ክፍት አድርጎ ባደረገልን መልካም አቀባበል ከችግርና ከሞት ታድጎናል” ሲሉ በሱዳን ግጭት ተሰደው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የተጠለሉ ሱዳናዊያን ስደተኞች ገለጹ።

ስደተኞቹ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተደረገላቸው አቀባበል እና ድጋፍ በስደት ወቅት ሊደርስባቸው ከሚችል እንግልት እና ስቃይ ታድጓቸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት አብዱልከሪም ሙሐመድ እንዳለው በሱዳን በተከሰተ ግጭት ምክንያት ከአገሩ ተሰዶ ላለፉት ሦስት ወራት በመተማ ዮሐንስ መጠለያ ጣቢያ እያሳለፈ ይገኛል።

እሱን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ወደ መተማ ሲገቡ በኢትዮጵያ መንግሥት መልካም አቀባበል እና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሶ ለእዚህም ያለውን ምስጋና ገልጿል።

ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ቀን ጀምሮ ምግብ፣ የመጠጥ ውኃ እና መጠለያ እያገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ አንዳንዴ የሚስተዋለው የምግብና የመድኃኒት እጥረት እንዲስተካከል ጠይቋል።

“ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ትልቅ አክብሮት እና ምስጋና አለኝ” ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ሱዳናዊ ተፈናቃይ አሚራ ሙሐመድ ናቸው።

ኢትዮጵያ ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት አድርጋ መቀበሏ በተለይ በስደት ወቅት በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ችግርና ሞት ማስቀረቷን ተናግረዋል።

በሱዳን በተፈጠረ ግጭት ከ13 የቤተሰብ አባላት ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ገልጸው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ በፍቅር እንደተቀበሏቸው ተናግረዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ በመጠለያው በቆዩባቸው ጊዜያት የምግብ እና የውኃ ድጋፍ እያገኙ ቢሆንም ለሕፃናት ልዩ እንክብካቤ በማድረግ በኩል የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ።

በተለይ ለሕፃናት የሚሆን የአልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁት ተፈናቃዩዋ፣ “በአካባቢው ስደተኞች በነፃነት መንቀሳቀስ የምንችልበት ሁኔታ ሊመቻችልን ይገባል” ብለዋል።

ሌላኛው ስደተኛ አብዱላዚዝ ሀሰን በበኩላቸው እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ያደረጉልን አቀባበል የባዕድነት ስሜት እንዳይሰማን አድርጓል።

“በስደት መጥተን የተደረገልን ወንድማዊ አቀባበል በአገሬ ያለው ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል፤ ለእዚህም ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው” ያሉት አብዱላዚዝ በመተማ መጠለያ ጣቢያ ምግብ፣ ውኃ እና ማረፊያ ከማቅረብ ጀምሮ የጤና ምርመራ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በመጠለያው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በተለያዩ ለጋሽ አካላት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በምግብ አቅርቦት በኩልም የለመድነው ምግብ ቢሆን ሲሉ ጠይቀዋል።

በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የመተማና አካባቢው የስደተኞች ካምፕ አስተባባሪ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው እንዳሉት በሱዳን በተከሰተው ግጭት ከስምንት በላይ ሀገራት ዜጎች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ስደተኞቹ የምግብ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የጤና እና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረው በቀጣይ ከተባበሩት መንግሥታት እና ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመሆን የስደተኞችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እንደሚሠራም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ተሰደው የመጡ ተፈናቀዮች በመጠለያ ካምፖች ይገኛሉ ያሉት አስተባባሪው በመተማና አካባቢውም እስካሁን ድረስ የተጠለሉ ስደተኞች ከ15 ሺሕ በላይ እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል ኢትዮጵያ ለሌሎች ትምህርት የሚሆን የቆየ ልምድ እንዳላት አስታውሰው በችግር ውስጥም ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መሆኗን ተናግረዋል።