ውጭ ከተላከ ቡና ከ896 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ሚያዝያ 25/2015 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቡና ወደ ውጭ ልካ ከ896 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ካሳሁን ገለታ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 243 ሺ 659 ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 1.19 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱንና 163 ሺ 666 ቶን የቡና ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም 896 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል ብለዋል የገበያ ልማትና ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚው።

በምርት መጠን የዕቅዱን 67 በመቶ፣ በገቢ ደግሞ 75 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመልክተው፤ በአፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸርም የ22 ነጥብ 4 በመቶ የምርት ቅናሽ ታይቷል ብለዋል፡፡

በገቢ ረገድ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ሲነጻጸር የ2.36 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ገቢ እንደተገኘ ገልጸዋል ሲል ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል፡፡