ስድስተኛው የ“ኢትዮ አረንጓዴ ፌሽታ” ፌስቲቫል በሰባት ከተሞች እንደሚካሄድ ተገለጸ

ኅዳር 22/2015 (ዋልታ) ስድስተኛው የ“ኢትዮ አረንጓዴ ፌሽታ“ አመታዊ የተፈጥሮ ፌስቲቫል በተለያዩ ሁነቶች በሰባት ከተሞች ከኅዳር 29  እስከ ግንቦት 30 ቀን 2015 እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

ፌስቲቫሉ ሀገራችን እያደረገችው ያለችውን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ወጣቱ ባህል እንዲያደርገው እና በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት ትስስር እንዲፈጥሩ የማስቻል አላማ ሰንቆ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

ዘንድሮ ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በሲዳማ ክልል ከተማ አስተዳደሮች የሚካሄድ ይሆናል፡፡

በሀገራችን አመታዊው የአረንጓዴ ልማት እና የጽዱ ባህል ፌስቲቫል መርኃ ግብር ብቸኛ የሚዲያ አጋር በመሆን ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ለተከታታይ ሁለት አመታት የሚቆይ አጋርነትን ወስዷል፡፡

በተቋማቱ መካከል የውል ስምምነቱን የኮርፖሬቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) እና የኢትዮ ግሪን ፌስት አዘጋጅ ታደሰ ልብሴ ተፈራርመዋል፡፡

በሰለሞን በየነ