ሶማሊያና ሶማሊላንድ ቢስማሙ የመጀመሪያዋ ተደሳች አገር ኢትዮጰያ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጥር 28/2016 (አዲስ ዋልታ) ሶማሊያና ሶማሊላንድ ቢስማሙ የመጀመሪያዋ ተደሳች አገር ኢትዮጵያ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም ባለፉት አስርት ዓመታት የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሞተዋል፤ ይህን የምናደርገው የሶማሊያ ሰላም የኢትዮጵያም ሰላም ስለሆነ ነው ብለዋል።

ለሶማሊያ አንድነት እንደዚህ መንግስት የሰራ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዚህም ማስረጃው ሶማሊያንና ሶማሊላንድን ለማስማማት ብዙ ጥረት መደረጉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያን መንግስት የመጉዳት ምንም ዓይነት ፍላጎት የላትም፤ ከሶማሊያ ወንድሞቻችን ጋር በጋራና በትብብር ማደግ እንፈልጋለን ሲሉ አክለዋለ፡፡

የሶማሊያ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ለመጋጨት የሚፈልግ አይመስለኝም፤ ነገር ግን ፍላጎት ያላቸው አካላት ሶማሊያን እንደ ውክልና ጦርነት ማካሄጃ ለመጠቀም የሚፈልጉ አሉ ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዚህ ተግባራቸው እኛ አንመችም ሲሉ አክለዋል።