ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ጥር 29/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ኮሞሮስ ዩኒየን ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሞሮስ ዩኒየን ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ እና የልዑካን ቡድናቸውን በጽሕፈት ቤታቸው በይፋዊ የአቀባበል ሥነ ስርዓት ተቀብለዋል።

ሁለቱ ልዑካን ቡድኖች በተካፈሉበት የሁለትዮሽ ውይይት የጋራ የዕድገት ርዕይ፣ ትብብር እና መከባበርን በተመለከተ አፅንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሬዝዳንት አዛሊ አሱማኒ በአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸው ያሳዩትን ምሳሌነት ያለው አመራር አድንቀው ከዚህ አንፃር በእርሳቸው አመራር ኅብረቱ ወደ ቡድን 20 መግባት የቻለበትን እርምጃ አውስተዋል።

ሁለቱ መሪዎች የጋራ ጥረት በፈተናዎች እና መፃዒ ዕድሎችን በመጠቀም ብሎም በመተለም ላይ ያለውን አስፈላጊነት በመቀበል ወደፊት ተመልካች በሆነ መንገድ በቀጣናዊ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል