ሶስት ዓመት ያልሞላው ህፃን አግተው 10 ሚሊዩን ብር ቤዛ የጠየቁ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

ኅዳር 14/2015 (ዋልታ) ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስን ይዘው በመሰወር 10 ሚሊዩን ብር ቤዛ ሲጠይቁ የነበሩ ሶስት ግለሰቦች በፈፀሙት ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተው፤ 1ኛ. መሪጌታ ምስጥሩ ይግዛው፣ 2ኛ. ዘውዲቱ ገብሬ እና 3ኛ ብሩክ ቸኮል በተባሉ ተከሰሾች ላይ ነው፡፡

ተከሳሾች ህጻን ሳሙኤልን በተቀናጀ አካሄድ ይዘውት መሰወራቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል ፖሊስ እና የደህንነት መስርያ ቤት ባካሄዱት ከፍተኛ ኦፕሬሽን ህጻኑን ከቤተሰቦቹ ጋር እንዲገናኝ ማድረግ ተችሏል፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሶስቱ ተከሳሾች ባቀናበሩት የወንጀል ድርጊት ሁለተኛ ተከሳሽ ከዚህ በፊት ተቀጥራ ስትሰራበት በነበረ የመኖሪያ ቤት ውስጥ እድሜው 2 ዓመት ከ11 ወር የሆነው ህጻን መኖሩን ለ1ኛ ተከሳሽ በጠቆመችው መሰረት ነው ወንጀሉ የተፈጸመው፡፡

በዚህም መሰረት ህፃን ሳሙኤል ዩሃንስን በ2ተኛ ተከሳሽ አማካኝነት ከቤት በማስወጣት እና ጠልፈው በመሰወር ከግል ተበዳይ ቤተሰቦች ብር ለመቀበል ተነጋግረው በድጋሚ ስራውን ለቃ ከቆየችበት የመኖሪያ ቤት ተቀጥራ እንድትገባ ይስማማሉ፡፡

ለዚህ ወንጀል ዓላማ ሲባልም 2ኛ ተከሳሽ ተመልሳ በቤት ሰራተኝነት በግል ተበዳይ ወላጆች መኖሪያ ቤት በመቀጠር ስትሰራ ከቆየች በኃላ ጥቅምት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክ/ከተማ ወረዳ 10 ክልል ህጻን ሳሙኤልን ማስቲካ ልግዛለት ብላ በማታለል ይዛው ከቤት በመውጣት በወቅቱ እዛው አካባቢ ይጠብቁዋት ከነበሩ 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመገናኘት ከአዲስ አበባ ውጭ ይዘውት ተሰውረዋል፡፡

በኋላም አንደኛ ተከሳሽ ለህጻኑ አባት በመደወል ህጻኑ ከእነሱ ጋር እንዳለ እና 10 ሚሊዮን ብር ካላመጡ እንደሚሸጡት እንዲሁም ሌሎች ማስፈራሪያዎች እየዛተ በመናገር ሲደራደር ሶስተኛ ተከሳሽም በተመሳሳይ በመደወል ብሩን ቶሎ ካልከፈላችሁ ህጻኑን ወደ መተማ ሊወሰዱት ነው በማለት ገንዘቡን አስፈራርተው ለመቀበል ሲደራደሩ ቆይተዋል፡፡

ፖሊስ ባደረገው ከፍተኛ ክትትል ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም 1ኛ ተከሳሽ በቁጥጥር የዋለ ሲሆን፤ የግል ተበዳይን ጨምሮ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በኦሮሚያ ክልል ኢጅሬ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ጨረቃ ሠፈር በሚገኝው 1ኛ ተከሳሽ ተከራይቶት በነበረው ቤት ውስጥ በፖሊስ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ጉዳዩ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የልዩ ልዩ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾች በፈፀሙት ከባድ ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅን መጥለፍ ወንጀል ኅዳር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን ተከትሎ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት ከባድ በመሆኑ ከጠበቃ ጋር ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ለኅዳር 20 ቀን/2015 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል::