ሸበሌ ባንክ አገልግሎቱን በይፋ ጀመረ

የካቲት 5/2015 (ዋልታ) ሸበሌ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በዛሬው እለት አገልግሎቱን በይፋ ጀምሯል።

የባንኩ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።

ቀደም ሲል የሶማሌ ክልል ማይክሮ ፋይናንስ የነበረው ተቋም ነው በአሁኑ ወቅት ወደ ባንክነት የተሸጋገረው።

በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ካፒታል አገልግሎቱን የጀመረው ሸበሌ ባንክ በሶማሌ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ከ20 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ነው የተገለጸው።

ባንኩ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ እና ሁሉን አካታች የባንክ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

በአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይም  የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የሶማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ም/ከንቲባ፣ የባንኩ የቦርድ አመራሮች እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ ገራድ፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሸበሌ ባንክን ጨምሮ በሀገሪቱ አራት ባንኮች ከወለድ ነፃ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውም ተመላክቷል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)