አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡት ምላሽ ከአውድ ውጭ መወሰዱን አስታወቁ

መጋቢት 22/2013 (ዋልታ) – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሰጡት ምላሽ ከአውድ ውጭ መወሰዱን አስታወቁ፡፡

መግለጫውን ተከትሎ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በፌዴሬሽን ሊዋሃዱ ነው በሚል በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ምን አቋም አለው የሚል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ለቀረበው ጥያቄም የተሰጠው ምላሽ አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በተለየ አውድ ማቅረባቸውን ነው የገለጹት፡፡

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኤርትራውያን ወገኖች ጉዳዩ ከአውድ ውጭ መወሰዱን እንዲያውቁ አሳስባለሁ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤርትራ ሉዓላዊነት የማይናወጥ አቋም አላቸው ነው ያሉት፡፡

እኔም በግለሰብ ደረጃ የኤርትራን ሉዓላዊነት አከብራለሁ ያሉት ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ ለተፈጠረው ብዥታ ይቅርታ እጠይቃለሁ ብለዋል፡፡

(ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር)