ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማምጣት ትምህርት ወሳኝ ሴክተር ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የካቲት 9/2016 (አዲስ ዋልታ) ቀጣይነት ያለውን እድገት ለማምጣት ትምህርት ወሳኝ ሴክተር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሁኑ የኛ የትምህርት ስርዓት ከምዕራባዊያኑ የተቀዳ እና የነሱን ኃያልነት የሚያሳይ እና የሚያስቀጥል እንዲሁም የኛን ባህልና አገር በቀል እውቀት እንዲቀጭጭ ያደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ በተለይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቋንቋ ሳይበግረን በቀላሉ መማር የሚቻልበት እድል የተፈጠረ ቢሆንም ፋይናንሻል ኢንቨስትመንት ዋናው ለትምህርት ተግዳሮት መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርቱ ዘርፍ ትኩረት አድርጋ ስትሰራ ቆይታለች ሲሉም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ የኮሙኒኬሽን ኔትወርክ፣ ባቡር፣ አየር መንገድ እና መሰል መገናኛዎችን እየገነባን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት እያጠናከርን እንገኛለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በብርሃኑ አበራ