37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ


የካቲት 11/2016 (አዲስ ዋልታ) 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎች በማሳለፍ ዛሬ ማለዳ ተጠናቋል።

ጉባኤው “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” ሕብረቱ ባዘጋጀው የ2024 መሪ ሀሳብ ከቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።

በጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ዲፕሎማቶች፣ የሕብረቱ ተቋማትና አደረጃጀቶች አመራሮች ተሳትፈዋል።

ጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው 44ኛው መደበኛ ስብሰባ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር አድርጓል።

ወቅታዊ የአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ሕብረት እየተደረጉ ያሉ ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ፣ የአፍሪካ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ስራዎች ጉባኤው ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል ይገኛሉ።

በተጨማሪም የአጀንዳ 2063 የመጀመሪያ ምዕራፍ የ10 ዓመት አፈጻጸምን በማየት የአጀንዳ 2063 የሁለተኛው ምዕራፍ የ10 ዓመት እቅድ ላይ ተወያይቶም አፅድቋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም ምርጫና ሌሎች ምክክር የተደረገባቸው ጉዳዮች ናቸው።

እንደኢዜአ ዘገባ ጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት ተቋማት፣ አደረጃጀቶችና ኮሚቴዎችን የስራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን አዳምጧል።