37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጀመረ

የካቲት 9/2016 (አዲስ ዋልታ) ለሁለት ቀናት የሚቆየው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀመረ።

በጉባኤው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳፋኪ ማህመት አፍሪካ የተጋረጠባትን ችግር ለመፍታት አፍሪካዊ አንድነት ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አፍሪካ በበርካታ ፈተናዎች እየተፈተነች በመሆኗ አህጉራዊ አንድነትን ለመፍጠር ጠንካራ የፓን አፍሪካኒዝም ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

አህጉራዊ የብሄርተኛነት ስሜት የአፍሪካን ችግሮች በአንድነት ለመፍታት ያስፈልጋል ያሉት ሊቀመንበሩ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እየተስተዋለ ቢሆንም እንደሚጠበቀው መሆን አልቻለም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመሪዎቹ ጉባኤ ዛሬ እና ነገ በሚኖረው ቆይታ 44ኛው የሕብረቱ የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት “ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት” በሚል ርዕስ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።

በብርሃኑ አበራ